lördag 20 november 2010

በጋሻው ደሳለኝ ፍርድ ቤት ቀረበ


  • ‹‹አዎ፣ ተሳድቤያለሁ፤ ወደፊትም እቀጥላለሁ›› (በጋሻው ደሳለኝ
  • 500 ብር ዋስትና አስይዟል፤ ለብይን ለኅዳር 23 ቀን እንዲቀርብ ታዟል
  • ‹‹ኀይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶችህ ዋሹብህ›› (ጥቂት ቲፎዞዎቹ የለበሱት ቲ-ሸርት)
 (ደጀ ሰላም፤ ኖቬምበር 5/2010፤ ጥቅምት 26/2003 ዓ.ም)በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማእከል የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት በጋሻው ደሳለኝ ዛሬ በድሬዳዋ ካውንስል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ዛሬ ጠዋት በተሠየመው ችሎት በተከሰሰበት የስም ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ የእምነት ክሕደት ቃሉን የተጠየቀው በጋሻው የተከሰሰበትን የንግግር ቃል መናገሩን አምኗል፡፡ በድምፅ የተቀረጸውን የንግግሩን ቅጂ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው በጋሻው፣ “ማኅበሩን እንደ ድርጅት ሳይሆን በማኅበረ ቅዱሳን ሽፋን የሚነግዱትን ነው የተሳደብኩት፤ በዚህ ደግሞ ወደፊትም አቀጥላለሁ፤ አላቆምም” በማለት ለችሎቱ ማስረዳቱ ተዘግቧል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ በተ ክህነት የዋና ሥራ አስኪያጁ ጽ/ቤት፣ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከአገልግሎት የታገደው በጋሻው ደሳለኝ መንገሻ እግዱን በመተላለፍ ሚያዝያ 19 ቀን 2002 ዓ.ም በድሬዳዋ ሳባ ደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ‹‹ንጉሥ በዙፋኑ አለ›› በሚል ርእስ ባሰማው ንግግር ብዙዎች በሚዲያ ‹ቢዘምቱበትም› እርሱን በዐውደ ምሕረት ከመቆም የከለከለው እንደሌለ ርእሱን ለራሱ ተርጉሞ ስለ ራሱ ከመናገር ያላፈረው ተከሳሹ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በጸደቀለት መተዳደሪያ ደንብ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ተደራጅቶ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ልማታዊ አገልግሎት እንዲሰጥ የተፈቀደለትን ማኅበረ ቅዱሳንን፣ “የወንድሞችን ደም ያፈሰሰ፣ አባቶችን በጋዜጣው ያዋረደ፣ ዘራፊ እና ሌባ” እንደ ሆነ ባልተገራ አንደበቱ መወንጀሉ ይታወሳል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ክሱን የሚያስረዱለትን ሦስት የሰው ምስክሮች እና የቪሲዲ ማስረጃዎች ያቀረበ ሲሆን ከሦስቱ ሰዎች ሁለቱ በሰጡት የምስክርነት ቃል ተከሳሹ በተጠቀሰው ወቅት የተባለውን ውንጀላ ሲናገር መስማታቸውን አስረድተዋል፤ የቀረበው የቪሲዲ ማስረጃም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑ ተገልጧል፡፡ ተከሳሹ የፈጸመውን የስም ማጥፋት ወንጀል በማመኑ፣ ይህም በዐቃቤ ሕግ በቀረበበት የሰው እና የሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም የቀጠረ ሲሆን በፖሊስ ተይዞ እንዲቀርብ የታዘዘው በጋሻውም የ500 ብር ዋስትና እንዲያሲዝ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡ “ወደ ውጭ አገር ስለምሄድ የብይኑ ቀጠሮ ቀን ይጠርልኝ” ብሏል በጋሻው ስለ ቀጣዩ ጊዜ ቀጠሮ ለችሎቱ አቅርቦት በነበረው ጥያቄ፡፡

እስከ ቀትር 6፡30 ድረስ በቆየው የፍርድ ቤቱ ውሎ ዐሥር ያህል የተከሳሹ ቲፎዞዎች፣ “ኀይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶችህ ዋሹብህ” የሚል ጥቅስ የሰፈረበት ቲ-ሸርት ለብሰው በዙሪያው ታይተዋል፡፡ ከቲፎዞዎቹ አንዳንዶቹ ማኅበረ ቅዱሳን በወንጌል እንደተጻፈው፣ “ከመክሰስ ለምን አይመክረውም ነበር” የሚል አስተያየት ሲሰጡ ተደምጧል፡፡ እነርሱ ይህን ይበሉ እንጂ ስም አጥፊው በጋሻው “በመሳደቤ እቀጥላለሁ” ከማለቱም በላይ ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው ሦስት ምስክሮች ሁለቱ የሰጡት ብቻ እንደሚበቃ በተናገረበት ወቅት፣ “ውሸቱን እንዳይደግምለት ነው” በማለት በችሎቱ ፊት በድፍረት መናገሩ ልበ ደንዳናነቱንና ላለመታረም ያለውን ዝንባሌ የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በሌላ በኩል ለበጋሻው ጥብቅና የቆሙለት የልምድ ነገረ ፈጅ ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ለማጋለጥ በተጋደሉት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች እና ወንድሞች ላይ የክስ ቻርጅ በማርቀቅ እና ‹በማማከር› የታወቁ መሆናቸው ሲታይ ተከሳሹ የቆመበትን ሰበካ ግልጽ ያደርገዋል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ በቅርቡ በእምነት ኑፋቄያቸው እና በሥነ ምግባር ብልሽታቸው የተነሣ ከድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት የተባረሩት ግለሰብም ሌላው የበጋሻው አጃቢ ነበሩ፡፡

በተያያዘ ዜና ‹‹መርከብ›› በሚል ስያሜ ባቋቋመው ‹ጋዜጣ› በማኅበረ ቅዱሳን የድሬዳዋ ማእከል ሰብሳቢ የሆኑትን የዲያቆን ድንበሩ ሰጠን ስም አላግባብ የሚያጠፋ ውንጀላ ያተመው ቀንደኛው የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ መሪጌታ ጽጌ ስጦታው ባለፈው ዓመት ቀርቦበት በነበረው አሳማኝ ማስረጃ የዘገባውን እውነተኛነት ሊያስረዳ/ክሱን ሊከላከል/ ባለመቻሉ፣ የሰባት ወር እስራት እና 2000 ብር ከተቀጣ በኋላ በቅጣቱ ተመጣጣኝነት ላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ይግባኝ ተከሳሹ በተጨማሪ ዐሥራ አንድ ወራት እስራት እና በተጨማሪ 16,000 ብር(በድምሩ ብር 18,000) የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል እንደተወሰነበት ለመረዳት ተችሏል፡፡