የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምስቱ የኦርየንታል (ምስራቃዊ) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክሪስቲያናት አንዱ ነው። ኢትዮጵያ የክርስትናን እምነት ከተቀበለችበት ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ጥር ፮ ቀን ፲፱፻፵፫ ዓ.ም (1951 እ.ኤ.አ.) ድረስ የእስክንድርያ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ክፍል ነበር። በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም ግን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባስልዮስ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ 2ኛ የጵጵስና ማዕረግ ተቀበሉ። ኢትዮጵያም፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እራሷን የቻለች ሆነች። ወደ 40-45 ሚሊዮን የሚቀርቡ ምእመናን ሲኖሩት ከምሥራቃዊ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ትልቁ ነው
«ተዋሕዶ» ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ሲሆን፡ ትርጒሙም «አንድ ሆኖ» ማለት ነው። ለዚሁም በዐረብኛ ተመሳሳይ ቃል «ታውሒድ» ሲባል በአንድ አምላክ ብቻ ማመን የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ያመለክታል። በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስትያናት ቃሉ የሚነካ የክርስቶስ ባሕርይ በ«ሰብዓዊ» እና በ«መለኮታዊ» ተለይቶ ሳይሆን አንድ ብቻ እንደሆነ የሚለው ጽኑ እምነት ነው።