måndag 8 november 2010

መዝሙር 73

1 ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው።
2 እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ።
3 የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና።
4 ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና።
5 እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም።
6 ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት።
7 ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ።
8 አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ።
9 አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ።
10 ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤
11 እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ።
12 እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ።
13 እንዲህም አልሁ። በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ።
14 ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው።
15 እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር።
16 አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ።
17 ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ።
18 በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው።
19 እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ።
20 ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።
21 ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና፤
22 እኔ የተናቅሁ ነኝ አላውቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ።
23 እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ።
24 በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ።
25 በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ?
26 የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው።
27 እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው።
28 ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።